ሕዝቅኤል 32:2-8 NASV

2 “የሰው ልጅ ሆይ፤ ለግብፅ ንጉሥ ለፈርዖን ሙሾ አውርድ፤ እንዲህም በለው፤“ ‘አንተ በሕዝቦች መካከል እንደ አንበሳ፣በባሕሮችም ውስጥ እንደ አስፈሪ አውሬ ነህ፤በወንዞችህ የምትንቦጫረቅ፣ውሃውን በእግርህ የምትመታ፣ምንጮችን የምታደፈርስ ነህ።

3 “ ‘ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤“ ‘ብዙ ሕዝብ ይዤ፣መረቤን በላይህ ላይ እጥላለሁ፤በመረቤም ጐትተው ያወጡሃል።

4 በምድር ላይ እጥልሃለሁ፤ሜዳም ላይ እዘረጋሃለሁ፤የሰማይ ወፎች ሁሉ እንዲሰፍሩብህ አደርጋለሁ፤የምድር አራዊት ሁሉ በመስገብገብ ይበሉሃል።

5 ሥጋህን በተራሮች ላይ እበታትነዋለሁ፤የተረፈውንም በየሸለቆው እሞላዋለሁ።

6 እስከ ተራሮች ባለው መንገድ ሁሉ፣በሚፈሰው ደምህ ምድሪቱን አርሳታለሁ፤ሸለቆዎችም በሥጋህ ይሞላሉ።

7 አንተን በማጠፋ ጊዜ ሰማያትን እሸፍናለሁ፤ከዋክብታቸውንም አጨልማለሁ፤ፀሓይን በደመና እሸፍናለሁ፤ጨረቃም ብርሃኗን አትሰጥም።

8 በሰማይ የሚያበሩትን ብርሃናት ሁሉ፣በአንተ ላይ አጨልማለሁ፤በምድርህ ላይ ጨለማን አመጣለሁ፤ይላል ጌታ እግዚአብሔር።