ሕዝቅኤል 32:4-10 NASV

4 በምድር ላይ እጥልሃለሁ፤ሜዳም ላይ እዘረጋሃለሁ፤የሰማይ ወፎች ሁሉ እንዲሰፍሩብህ አደርጋለሁ፤የምድር አራዊት ሁሉ በመስገብገብ ይበሉሃል።

5 ሥጋህን በተራሮች ላይ እበታትነዋለሁ፤የተረፈውንም በየሸለቆው እሞላዋለሁ።

6 እስከ ተራሮች ባለው መንገድ ሁሉ፣በሚፈሰው ደምህ ምድሪቱን አርሳታለሁ፤ሸለቆዎችም በሥጋህ ይሞላሉ።

7 አንተን በማጠፋ ጊዜ ሰማያትን እሸፍናለሁ፤ከዋክብታቸውንም አጨልማለሁ፤ፀሓይን በደመና እሸፍናለሁ፤ጨረቃም ብርሃኗን አትሰጥም።

8 በሰማይ የሚያበሩትን ብርሃናት ሁሉ፣በአንተ ላይ አጨልማለሁ፤በምድርህ ላይ ጨለማን አመጣለሁ፤ይላል ጌታ እግዚአብሔር።

9 በማታውቀው ምድር፣በሕዝቦች መካከል ያንተን ጥፋት ሳመጣ፣የብዙ ሕዝብን ልብ አስጨንቃለሁ።

10 ሕዝቦች በአንተ ላይ ከደረሰው የተነሣ እንዲደነግጡ አደርጋለሁ፤ሰይፌን በፊታቸው ስነቀንቅ፣በአንተ ላይ ከደረሰው ሁኔታ የተነሣ ንጉሦቻቸው ይንቀጠቀጣሉ።አንተ በምትወድቅበት ቀን፣እያንዳንዳቸው ስለ ራሳቸው ሕይወት በመፍራት፣በየቅጽበቱ ይርበደበዳሉ።