ሕዝቅኤል 32:8-14 NASV

8 በሰማይ የሚያበሩትን ብርሃናት ሁሉ፣በአንተ ላይ አጨልማለሁ፤በምድርህ ላይ ጨለማን አመጣለሁ፤ይላል ጌታ እግዚአብሔር።

9 በማታውቀው ምድር፣በሕዝቦች መካከል ያንተን ጥፋት ሳመጣ፣የብዙ ሕዝብን ልብ አስጨንቃለሁ።

10 ሕዝቦች በአንተ ላይ ከደረሰው የተነሣ እንዲደነግጡ አደርጋለሁ፤ሰይፌን በፊታቸው ስነቀንቅ፣በአንተ ላይ ከደረሰው ሁኔታ የተነሣ ንጉሦቻቸው ይንቀጠቀጣሉ።አንተ በምትወድቅበት ቀን፣እያንዳንዳቸው ስለ ራሳቸው ሕይወት በመፍራት፣በየቅጽበቱ ይርበደበዳሉ።

11 “ ‘ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላልና፤“ ‘የባቢሎን ንጉሥ ሰይፍ፣በአንተ ላይ ይመጣል።

12 ከሕዝቦች ሁሉ እጅግ ጨካኝ በሆኑት፣በኀያላን ሰዎች ሰይፍ፣ያከማቸኸው ሰራዊት እንዲወድቅ አደርጋለሁ፤የግብፅን ኵራት ያንኰታኵታሉ፤የሰራዊቷም ብዛት ይጠፋል፤

13 ብዙ ውሃ ባለበት አጠገብ ያለውን፣የከብት መንጋዋን አጠፋለሁ፤ከእንግዲህ የሰው እግር አይረጋግጠውም፤የከብትም ኮቴ አያደፈርሰውም።

14 ከዚያም ውሆቿን አጠራለሁ፤ወንዞቿም እንደ ዘይት እንዲፈሱ አደርጋለሁ፤ይላል ጌታ እግዚአብሔር።