16 ከሠራው ኀጢአት አንዱም አይታሰብበትም፤ ቀናውንና ትክክለኛውን አድርጓልና፤ በእርግጥ በሕይወት ይኖራል።
17 “ይህም ሆኖ የአገርህ ሰዎች፣ ‘የጌታ መንገድ ቀና አይደለችም’ ይላሉ፤ ቀና ያልሆነው ግን የእነርሱ መንገድ ነው።
18 ጻድቅ ሰው የጽድቁን ሥራ ትቶ ክፉ ነገር ቢያደርግ፣ ስለ ኀጢአቱ ይሞታል።
19 ክፉም ሰው ከክፉ ሥራው ተመልሶ ቀናውንና ትክክለኛውን ነገር ቢያደርግ፣ ይህን በማድረጉ በሕይወት ይኖራል።
20 ይሁን እንጂ የእስራኤል ቤት ሆይ፤ ‘የጌታ መንገድ ቀና አይደለችም’ ትላላችሁ፤ ነገር ግን በእያንዳንዳችሁ ላይ እንደ መንገዳችሁ እፈርድባችኋለሁ።”
21 በተማረክን በዐሥራ ሁለተኛው ዓመት፣ በዐሥረኛው ወር፣ በአምስተኛው ቀን፣ ከኢየሩሳሌም ያመለጠ አንድ ሰው ወደ እኔ መጥቶ፣ “ከተማዪቱ ወደቀች!” አለኝ።
22 ሰውየው ከመድረሱ በፊት በነበረው ምሽት፣ የእግዚአብሔር እጅ በላዬ ላይ ነበረች፤ በማለዳም ሰውየው ወደ እኔ ከመምጣቱ በፊት እግዚአብሔር አፌን ከፈተ፤ አፌም ተከፈተ፤ ከዚያ በኋላ ዝም አላልሁም።