ሕዝቅኤል 34:16-22 NASV

16 የጠፉትን እፈልጋለሁ፤ የባዘኑትንም እመልሳለሁ። የተጐዱትን እጠግናለሁ፤ የደከሙትንም አበረታለሁ፤ የወፈረውንና የበረታውን ግን አጠፋለሁ። መንጋውን በፍትሕ እጠብቃለሁ።

17 “ ‘መንጋዬ ስለ ሆናችሁት ስለ እናንተ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ በበግና በበግ መካከል፣ በአውራ በግና በአውራ ፍየል መካከል እፈርዳለሁ።

18 በለምለሙ መስክ ላይ መመገቡ አይበቃችሁምን? የተረፈውን መሰማሪያችሁን ደግሞ በእግራችሁ መረጋገጥ ይገባችኋልን? ንጹሕ ውሃ መጠጣቱ አይበቃችሁምን? የተረፈውንስ በእግራችሁ ማደፍረስ ይገባችኋልን?

19 መንጋዬ የረጋገጣችሁትን መመገብና በእግራችሁ ያደፈረሳችሁትን መጠጣት ይገባዋልን?

20 “ ‘ስለዚህ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላቸዋል፤ “እነሆ እኔ ራሴ በሰባው በግና በከሳው በግ መካከል እፈርዳለሁ።

21 ደካሞቹን በጎች በጐናችሁና በትከሻችሁ ስለምት ገፈትሩ፣ እስኪባረሩም ድረስ በቀንዳችሁ ስለምትወጓቸው፣

22 እኔ መንጋዬን አድናለሁ፤ ከእንግዲህ ለንጥቂያ አይዳረጉም፤ በአንዱ በግና በሌላውም በግ መካከል እፈርዳለሁ።