ሕዝቅኤል 34:23-29 NASV

23 በእነርሱ ላይ አንድ እረኛ፣ ባሪያዬን ዳዊትን አቆማለሁ፤ እርሱም ያሰማራቸዋል፤ እረኛቸውም ይሆናል።

24 እኔ እግዚአብሔር አምላካቸው እሆናለሁ፤ ባሪያዬ ዳዊትም በመካከላቸው ገዥ ይሆናል፤ እኔ እግዚአብሔር ተናግሬአለሁ።”

25 “ ‘ከእነርሱ ጋር የሰላም ቃል ኪዳን እገባለሁ፤ ከዚያም ምድሪቱን ከዱር አራዊት ነጻ አደርጋለሁ፤ እነርሱም በምድረ በዳ ይኖራሉ፤ በደንም ውስጥ በሰላም ይተኛሉ።

26 እነርሱንና በኰረብታዬ ዙሪያ ያሉትን ስፍራዎች እባርካለሁ። በወቅቱም ዝናብ አወርድላቸዋለሁ፤ ዝናቡም የበረከት ዝናብ ይሆናል።

27 የየሜዳው ዛፍ ፍሬ ይሰጣል፤ መሬቱም እህል ያበቅላል። ሕዝቡም በምድሪቱ ላይ በሰላም ይኖራሉ። የቀንበሮቻቸውን ማነቆ ሰብሬ በባርነት ከገዟቸው እጅ ሳድናቸው፣ እኔ እግዚአብሔር እንደሆንሁ ያውቃሉ።

28 ከእንግዲህ ለሌሎች ሕዝቦች ንጥቂያ አይዳረጉም፤ የዱር አራዊት አይቦጫጭቋቸውም፤ በሰላም ይኖራሉ፤ የሚያስፈራቸውም አይኖርም።

29 ከእንግዲህ በምድሪቱ ላይ የራብ ተጠቂ እንዳይሆኑ፣ የአሕዛብንም ስድብ እንዳይሸከሙ ፍሬ በመስጠት የታወቀውን መሬት እሰጣቸዋለሁ።