3 እንዲህም በል፤ ‘ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ የሴይር ተራራ ሆይ፤ በአንተ ላይ ተነሥቻለሁ፤ እጄን በአንተ ላይ እዘረጋለሁ፤ ባድማና ጠፍ አደርግሃለሁ።
4 ከተሞችህን ፍርስራሽ አደርጋቸዋለሁ፤ ባድማ ትሆናለህ፤ ከዚያም እኔ እግዚአብሔር እንደሆንሁ ታውቃለህ።
5 “ ‘እስራኤላውያን ቅጣታቸው እጅግ መራራ ከሆነ ደረጃ ላይ ደርሶ ፍዳቸውን በሚቀበሉበት ጊዜ፣ የጥንቱን ቂም ቋጥረህ ለሰይፍ ስለ ዳረግሃቸው፤
6 በሕያውነቴ እምላለሁ፤ ይላል ጌታ እግዚአብሔር፤ ለደም ማፍሰስ አሳልፌ እሰጥሃለሁ፤ እርሱም ያሳድድሃል። ደም ማፍሰስን ስላልጠላህ፣ ደም ማፍሰስ ያሳድድሃል።
7 የሴይርን ተራራ ባድማና ጠፍ አደርጋለሁ፤ በእርሱም ላይ የሚወጡትንና የሚወርዱትን አስቀራለሁ።
8 ተራሮችህን በሬሳ እሞላለሁ፤ በሰይፍ የተገደሉት ሁሉ በተራሮችህ፣ በሸለቆዎችህና በውሃ መውረጃዎችህ ሁሉ ላይ ይወድቃሉ።
9 ለዘላለም ባድማ አደርግሃለሁ፤ ከተሞችህ መኖሪያ አይሆኑም። ከዚያም እኔ እግዚአብሔር እንደሆንሁ ታውቃላችሁ።