ሕዝቅኤል 37:4-10 NASV

4 ከዚያም እንዲህ አለኝ፤ “ለእነዚህ ዐጥንቶች ትንቢት ተናገር፤ እንዲህም በላቸው፤ ‘እናንት ደረቅ ዐጥንቶች፤ የእግዚአብሔርን ቃል ስሙ!

5 ጌታ እግዚአብሔር ለእነዚህ፤ ዐጥንቶች እንዲህ ይላል፤ “እስትንፋስ አገባባችኋለሁ፤ እናንተም በሕይወት ትኖራላችሁ።

6 ጅማት አደርግላችኋለሁ፤ ሥጋ አለብሳችኋለሁ፤ በቆዳ እሸፍናችኋለሁ፤ በውስጣችሁም እስትንፋስ አገባባችኋለሁ፤ በሕይወት ትኖራላችሁ፤ እኔም እግዚአብሔር እንደሆንሁ ታውቃላችሁ።” ’

7 ስለዚህ እንደ ታዘዝሁት ትንቢት ተናገርሁ፤ ትንቢቱን በምናገርበትም ጊዜ የኵሽ ኵሽታ ድምፅ ተሰማ፤ ዐጥንቶቹም አንድ ላይ ሆኑ፤ ዐጥንት ከዐጥንት ጋር ተጋጠመ።

8 እኔም ተመለከትሁ፤ ጅማት ነበረባቸው፤ ሥጋም በላያቸው ታየ፤ ቆዳም ሸፍኖአቸዋል፤ እስትንፋስ ግን በውስጣቸው አልነበረም።

9 ከዚያም እንዲህ አለኝ፤ “የሰው ልጅ ሆይ፤ ለነፋሱ ትንቢት ተናገር፤ ትንቢት ተናገር፤ እንዲህም በለው፤ ‘ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ “ነፋስ ሆይ፤ ከአራቱ ነፋሳት ዘንድ ና፤ በሕይወት እንዲኖሩም በእነዚህ በተገደሉት ላይ እፍ በልባቸው።” ’

10 ስለዚህም እንዳዘዘኝ ትንቢት ተናገርሁ፤ እስትንፋስም ገባባቸው፤ ሕያዋንም ሆኑ፤ እጅግ ታላቅ ሰራዊት ሆነው በእግራቸው ቆሙ።