ሕዝቅኤል 39:17-23 NASV

17 “ ‘የሰው ልጅ ሆይ፤ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ‘ማንኛውንም ዐይነት ወፍና የዱር አራዊት ሁሉ ጥራ፤ እንዲህም በላቸው፤ “ከየአቅጣጫው ተሰብስባችሁ እኔ ወደማዘጋጅላችሁ መሥዋዕት ኑ፤ ይህም በእስራኤል ተራሮች ላይ የሚሆን ታላቁ መሥዋዕት ነው። በዚያ ሥጋ ትበላላችሁ፤ ደምም ትጠጣላችሁ።

18 እንደ አውራ በግና እንደ ጠቦት፤ እንደ ፍየልና እንደ ወይፈን፣ የኀያላን ሰዎችን ሥጋ ትበላላችሁ፤ የምድርንም መሳፍንት ደም ትጠጣላችሁ፤ እነዚህ ሁሉ የሰቡ የባሳን ከብቶች ናቸው።

19 እኔ በማዘጋጅላችሁም መሥዋዕት እስክትጠግቡ ስብ ትበላላችሁ፤ እስክትሰክሩም ደም ትጠጣላችሁ።

20 በገበታዬም ፈረሶችንና ፈረሰኞችን፣ ኀያላን ሰዎችንና ከየወገኑ የሆኑትን ወታደሮች እስክትጠግቡ ትበላላችሁ፤” ይላል ጌታ እግዚአብሔር።’

21 “ክብሬን በአሕዛብ መካከል እገልጣለሁ፤ አሕዛብም ሁሉ በእነርሱ ላይ ያመጣሁትን ቅጣትና በላያቸው ላይ የጫንሁትን እጅ ያያሉ።

22 ከዚያን ጊዜ ጀምሮ የእስራኤል ቤት እኔ እግዚአብሔር፣ አምላካቸው እንደሆንሁ ያውቃሉ።

23 አሕዛብም የእስራኤል ሕዝብ ለእኔ ታማኞች ባለመሆን ከሠሩት ኀጢአት የተነሣ እንደ ተሰደዱ ያውቃሉ፤ ስለዚህ ፊቴን ከእነርሱ ሰወርሁ፤ ለጠላቶቻቸው አሳልፌ ሰጠኋቸው፤ ሁሉም በሰይፍ ወደቁ።