ሕዝቅኤል 39:3-9 NASV

3 በግራ እጅህ ያለውን ቀስትህን እመታለሁ፤ በቀኝ እጅህ የያዝሃቸውንም ፍላጾች አስረግፍሃለሁ።

4 አንተና ወታደሮችህ ሁሉ፣ ከአንተም ጋር ያሉ ሕዝቦች በእስራኤል ተራሮች ላይ ትወድቃላችሁ። ነጣቂ አሞሮችና የዱር አራዊት ይበሏችሁ ዘንድ አሳልፌ እሰጣችኋለሁ።

5 አውላላ ሜዳ ላይ ትወድቃለህ፤ እኔ ተናግሬአለሁና፤ ይላል ጌታ እግዚአብሔር።

6 በማጎግና ያለ ሥጋት በባሕር ዳርቻ በሚኖሩት ላይ እሳት እሰዳለሁ፤ እነርሱም እኔ እግዚአብሔር እንደሆንሁ ያውቃሉ።”

7 “ ‘ቅዱሱ ስሜ በሕዝቤ በእስራኤል ዘንድ እንዲታወቅ አደርጋለሁ፤ ከእንግዲህ ወዲያ ቅዱስ ስሜ እንዲናቅ፣ እንዲቃለል አልፈልግም፤ አሕዛብም እኔ እግዚአብሔር የእስራኤል ቅዱስ እንደሆንሁ ያውቃሉ።

8 እነሆ ይመጣል፤ በእርግጥም ይሆናል፤ ይላል ጌታ እግዚአብሔር፤ ያ ያልሁት ቀን ይህ ነው።

9 “ ‘ከዚያም በእስራኤል ከተሞች የሚኖሩ ሁሉ ወጥተው የጦር መሣሪያውን፣ ትልልቁንና ትንንሹን ጋሻ፣ ቀስቱን፣ ፍላጻውን፣ የጦር ዱላውንና ጦሩን ሰብስበው ማገዶ በማድረግ ያነዱታል፤ ሰባት ዓመት ይማግዱታል።