ሕዝቅኤል 39:7-13 NASV

7 “ ‘ቅዱሱ ስሜ በሕዝቤ በእስራኤል ዘንድ እንዲታወቅ አደርጋለሁ፤ ከእንግዲህ ወዲያ ቅዱስ ስሜ እንዲናቅ፣ እንዲቃለል አልፈልግም፤ አሕዛብም እኔ እግዚአብሔር የእስራኤል ቅዱስ እንደሆንሁ ያውቃሉ።

8 እነሆ ይመጣል፤ በእርግጥም ይሆናል፤ ይላል ጌታ እግዚአብሔር፤ ያ ያልሁት ቀን ይህ ነው።

9 “ ‘ከዚያም በእስራኤል ከተሞች የሚኖሩ ሁሉ ወጥተው የጦር መሣሪያውን፣ ትልልቁንና ትንንሹን ጋሻ፣ ቀስቱን፣ ፍላጻውን፣ የጦር ዱላውንና ጦሩን ሰብስበው ማገዶ በማድረግ ያነዱታል፤ ሰባት ዓመት ይማግዱታል።

10 ከሜዳ ላይ ዕንጨት መልቀም፣ ከዱርም ዛፍ መቍረጥ አያስፈልጋቸውም፤ የጦር መሣሪያቸውን በመማገድ ይጠቀማሉና። የዘረፏቸውን ይዘርፋሉ፤ የበዘበዟቸውን ይበዘብዛሉ፤ ይላል ጌታ እግዚአብሔር።

11 “ ‘በዚያ ቀን ሰዎች በምሥራቅ በኩል ወደ ባሕሩ በሚጓዙበት ሸለቆ፣ ለጎግ የመቃብር ስፍራ በእስራኤል እሰጠዋለሁ። ጎግና ሰራዊቱ ሁሉ በዚያ ስለሚቀበሩ፣ የተጓዦችን መንገድ ይዘጋሉ፤ ስለዚህም የሐሞን ጎግ ሸለቆ ይባላል።

12 “ ‘ምድሪቱን ለማጽዳት፣ የእስራኤል ቤት ሰዎች ሰባት ወር ሙሉ ይቀብሯቸዋል።

13 የምድሪቱ ሰዎች ሁሉ ይቀብሯቸዋል፤ እኔ የምከብርበትም ዕለት የመታሰቢያ ቀን ይሆናቸዋል፤ ይላል ጌታ እግዚአብሔር።