1 በተሰደድን በሃያ አምስተኛው ዓመት፣ በዓመቱ መጀመሪያ፣ በዐሥረኛው ቀን፣ ከተማዪቱ በወደቀች በዐሥራ አራተኛው ዓመት፣ በዚያው ዕለት የእግዚአብሔር እጅ በላዬ ነበር፤ እርሱም ወደዚያ ወሰደኝ።
2 በእግዚአብሔር ራእይ ወደ እስራኤል ምድር አመጣኝ፤ ከፍ ባለ ተራራ ላይ አኖረኝ፤ ከተራራውም በስተ ደቡብ፣ ከተማ የሚመስሉ ሕንጻዎች ነበሩ።
3 ወደዚያ ወሰደኝ፤ እነሆ መልኩ ናስ የሚመስል ሰው አየሁ፤ እርሱም የሐር ገመድና መለኪያ ዘንግ በእጁ ይዞ በመግቢያው በር ላይ ቆሞ ነበር።
4 ሰውየውም እንዲህ አለኝ፤ “የሰው ልጅ ሆይ፤ በዐይንህ እይ፤ በጆሮህ ስማ፤ የማሳይህንም ሁሉ ልብ ብለህ አስተውል፤ ወደዚህ የመጣኸው ለዚህ ነውና ያየኸውንም ሁሉ ለእስራኤል ቤት ንገር።”
5 የቤተ መቅደሱን ዙሪያ ሙሉ በሙሉ የከበበ ቅጥር አየሁ፤ በሰውየውም እጅ ርዝመቱ ስድስት ክንድ የሆነ መለኪያ ዘንግ አየሁ፤ እያንዳንዱ ክንድ፣ አንድ ክንድ ከስንዝር ነበር፤ እርሱም ቅጥሩን ለካው፤ ስፋቱ አንድ መለኪያ ዘንግ ሲሆን፣ ቁመቱም እንዲሁ አንድ መለኪያ ዘንግ ነበር።