ሕዝቅኤል 40:12-18 NASV

12 በእያንዳንዱ ዘብ ቤት ፊት ለፊት ከፍታው አንድ ክንድ የሆነ መከለያ የግንብ ዐጥር አለ፤ የዘብ ቤቶቹም ስፋት እኩል በኩል ስድስት ክንድ ነበር።

13 ከዚያም ከዘብ ቤቱ የኋላ ግድግዳ ጀምሮ እስከ ሌላው ጫፍ ድረስ ያለውን የመግቢያ በር ለካ፤ ከአንዱ መከለያ ግድግዳ እስከ ሌላው መከለያ ግድግዳ ያለው ርቀት ሃያ አምስት ክንድ ነበር።

14 በመግቢያው በር ዙሪያ ባሉት ወጣ ወጣ ባሉት ግንቦች ሁሉ ፊት ለፊት ያለውን ቦታ ለካ፤ ሥልሳ ክንድም ነበር። የተለካውም ከአደባባዩ ፊት ለፊት እስካለው መተላለፊያ በረንዳ ድረስ ነበር።

15 ከበሩ መግቢያ እስከ መተላለፊያ በረንዳው መጨረሻ ድረስ ያለው ርቀት አምሳ ክንድ ነበር።

16 ክፍሎቹ እንደ መተላለፊያ በረንዳዎቹ ከግራና ከቀኝ በኩል ትንንሽ መስኮቶች አሏቸው። በዙሪያው ያሉ መስኮቶች በመግቢያው በር ፊት ለፊት የነበሩ ሲሆን፣ በእያንዳንዱ ክፍል ግራና ቀኝ ግድግዳ ላይ ደግሞ የዘንባባ ዛፍ ተቀርጾበታል።

17 ከዚያም ወደ ውጩ አደባባይ አመጣኝ፤ እዚያም በአደባባዩ ዙሪያ የተሠሩ ክፍሎችና ድንጋይ የተነጠፈበት መመላለሻ አየሁ፤ በመመላለሻውም ዙሪያ ሠላሳ ክፍሎች ነበሩ።

18 የታችኛው ንጣፍ ወለል ከመግቢያው በር ጋር ተያይዞ የተሠራ ሲሆን፣ ስፋቱ እንደ በሮቹ ርዝመት መጠን ነበር።