ሕዝቅኤል 40:18-24 NASV

18 የታችኛው ንጣፍ ወለል ከመግቢያው በር ጋር ተያይዞ የተሠራ ሲሆን፣ ስፋቱ እንደ በሮቹ ርዝመት መጠን ነበር።

19 ከዚያም ከታችኛው መግቢያ በር ፊት ጀምሮ እስከ ውስጠኛው አደባባይ ፊት ድረስ ያለውን ርቀት ለካ፤ በምሥራቅም ሆነ በሰሜን በኩል ያለው ርቀት አንድ መቶ ክንድ ነበር።

20 ከዚያም በሰሜን ትይዩ ያለውን፣ ወደ ውጩ አደባባይ የሚያመራውን በር ርዝመትና ወርድ ለካ።

21 እንደ መጀመሪያው በር ሁሉ ይኸኛውም በየጐኑ ያሉት ሦስት ሦስት የዘብ ቤቶች፣ በየመካከሉ ወጣ ወጣ ያሉ ግንቦችና መተላለፊያ በረንዳዎቹ መጠናቸው እኩል ነበር። ርዝመቱ አምሳ ክንድ፣ ወርዱም ሃያ አምስት ክንድ ነበር።

22 መስኮቶቹ፣ መተላለፊያ በረንዳዎቹና የዘንባባ ዛፍ ቅርጾቹ ልካቸው በምሥራቁ በር ካሉት ጋር ተመሳሳይ ነበር። ወደዚያ የሚያመሩ ሰባት ደረጃዎች አሉ፤ መተላለፊያ በረንዳዎቹም ከእነርሱ ጋር ትይዩ ነበር።

23 ልክ በምሥራቅ በኩል እንዳለው ሁሉ፣ ከሰሜኑ በር ጋር ትይዩ የሆነ ወደ ውስጠኛው አደባባይ የሚያመራ በር አለ። ከአንዱ በር እስከ ሌላኛው በር ያለውን ለካው፤ ይህም አንድ መቶ ክንድ ነበር።

24 ከዚያም ወደ ደቡብ አቅጣጫ መራኝ፤ እዚያም ፊቱን ወደ ደቡብ ያደረገ በር አየሁ፤ እርሱም የውስጠኛውን ግድግዳና መተላለፊያ በረንዳውን ለካ፤ የእነዚህም መጠን እንደ ሌሎቹ በሮች ነበር።