1 ከዚያም ወደ መቅደሱ አገባኝ፤ ዐምዶቹንም ለካ፤ የዐምዶቹም ወርድ በአንዱ በኩል ስድስት ክንድ፣ በሌላውም በኩል ስድስት ክንድ ነበር።
2 የመግቢያውም በር ወርድ ዐሥር ክንድ ሲሆን፣ በግራና በቀኝ በኩል ወጣ ወጣ ያሉት ግንቦች ወርድ አምስት ክንድ ነበር። ደግሞም የውስጡን መቅደስ ለካ፤ ርዝመቱ አርባ ክንድ፣ ወርዱም ሃያ ክንድ ነበር።
3 ከዚያም ወደ ውስጥ ገባ፤ የመግቢያውን ዐምዶች ለካ፤ የእያንዳንዱም ወርድ ሁለት ክንድ ነበር። የመግቢያውም ወርድ ስድስት ክንድ ሲሆን፣ ግራና ቀኝ ወጣ ወጣ ያሉት ግንቦች ወርድ ደግሞ ሰባት ክንድ ነበር።
4 እርሱም የውስጠኛውን መቅደስ ርዝመት ለካ፤ ሃያ ክንድ ነበር፤ ወርዱም የውጪውን ግድግዳ ጨምሮ ሃያ ክንድ ነበር፤ እርሱም፣ “ይህ ቅድስተ ቅዱሳን ነው” አለኝ።