ሕዝቅኤል 41:20-26 NASV

20 ከወለሉ አንሥቶ ከመግቢያው በላይ እስካለው ስፍራ ድረስ፣ የውስጡ መቅደስ የውጭ ግድግዳ ላይ ኪሩቤልና የዘንባባ ዛፍ ተቀርጾአል።

21 የውስጡ መቅደስ በር መቃን ባለ አራት ማእዘን ነበር፤ ከቅድስተ ቅዱሳኑም ፊት ለፊት ያለው በር እንዲሁ ባለ አራት ማእዘን ነበር።

22 ሦስት ክንድ ቁመት፣ ሁለት ክንድ ወርድ፣ ሁለት ክንድ ርዝመት ያለው የዕንጨት መሠዊያ ነበር፤ ማእዘኖቹ፣ መሠረቱና ጐኖቹ ሁሉ ከዕንጨት የተሠሩ ነበሩ። ሰውዬውም፣ “ይህች በእግዚአብሔር ፊት ያለች ገበታ ናት” አለኝ።

23 የውስጡ መቅደስና ቅድስተ ቅዱሳኑ እያንዳንዳቸው ሁለት ሁለት በር አላቸው፤

24 እያንዳንዱ በር መካከሉ ላይ በመታጠፊያ የተያያዙ መዝጊያዎች አሉት።

25 በግንቦቹ ላይ እንዳለው ሁሉ በውስጡ መቅደስ በሮችም ላይ ኪሩቤልና የዘንባባ ዛፎች ተቀርጸዋል፤ በመተላለፊያ በረንዳውም ፊት ለፊት የዕንጨት መዝጊያ ተንጠልጥሎአል።

26 በመተላለፊያ በረንዳውም ግራና ቀኝ ግንብ ላይ የዘንባባ ዛፍ ቅርጽ ያለባቸው ጠባብ መስኮቶች ነበሩ። ግራና ቀኝ ያሉት ክፍሎችም በደረጃው በኩል የሚሸፍን ጣሪያ ነበራቸው።