ሕዝቅኤል 44:1-7 NASV

1 ከዚያም ያ ሰው ለምሥራቅ ትይዩ ወደ ሆነው በስተ ውጩ ወዳለው ወደ መቅደሱ በር መልሶ አመጣኝ፤ ተዘግቶም ነበር።

2 እግዚአብሔር እንዲህ አለኝ፤ “ይህ በር እንደ ተዘጋ ይኖራል፤ መከፈት የለበትም፤ ማንም አይገባበትም፤ የእስራኤል አምላክእግዚአብሔር ገብቶበታልና፤ ተዘግቶ ይኖራል።

3 በእግዚአብሔር ፊት ይበላ ዘንድ በመግቢያው በር ገብቶ ውስጥ ሊቀመጥ የሚችለው ገዡ ራሱ ብቻ ነው፤ በመግቢያው መተላለፊያ በረንዳ እንደ ገባ መውጣትም የሚችለው በዚያው ነው።”

4 ከዚያም ያ ሰው በሰሜኑ በር በኩል ወደ ቤተ መቅደሱ ፊት ለፊት አመጣኝ፤ እኔም ተመለከትሁ፤ የእግዚአብሔርም ክብር የእግዚአብሔርን ቤተ መቅደስ ሞልቶት አየሁ፤ በግንባሬም ተደፋሁ።

5 እግዚአብሔር እንዲህ አለኝ፤ “የሰው ልጅ ሆይ፤ ስለ እግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ሥርዐት የምነግርህን ሁሉ በጥንቃቄ አስተውል፤ በሚገባ አድምጥ፤ ልብም በለው። የቤተ መቅደሱን መግቢያና የመቅደሱን መውጫዎች ሁሉ አስተውል፤

6 ለዐመፀኛው የእስራኤል ቤት እንዲህ በል፤ ‘ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ “የእስራኤል ቤት ሆይ፤ አስጸያፊ ሥራችሁ ከእንግዲህ ያብቃ!

7 ከአስጸያፊ ሥራችሁም ሌላ ምግብ፣ ስብና ደም ስታቀርቡ ልባቸውንና ሥጋቸውን ያልተገረዙትን እንግዶች ወደ መቅደሴ በማስገባት ቤተ መቅደሴን አረከሳችሁ፤ ቃል ኪዳኔንም አፈረሳችሁ።