13 እንደ ካህናት ያገለግሉኝ ዘንድ ወደ እኔ አይቀርቡም፤ ወይም ቅዱስ ወደ ሆነው ነገሬ ሁሉ፣ ወይም እጅግ ወደ ተቀደሱ መሥዋዕቶቼ አይቀርቡም፤ የአስጸያፊ ድርጊታቸውን ኀፍረት ይሸከማሉ።
14 ያም ሆኖ የቤተ መቅደሱን ሥራ በኀላፊነት እንዲሠሩ፣ በውስጡ የሚከናወኑትንም ሥራዎች ሁሉ እንዲቈጣጠሩ አደርጋቸዋለሁ።
15 ‘ “ነገር ግን እስራኤላውያን ከመንገዴ ስተው በወጡ ጊዜ፣ የመቅደሴን ሥራ በታማኝነት ያከናወኑት የሳዶቅ ዘርና ሌዋውያን የሆኑት፣ በፊቴ ቀርበው ያገለግሉኛል፤ በፊቴ ቆመው የስብና የደም መሥዋዕት ያቀርቡልኛል፤ ይላል ጌታ እግዚአብሔር።
16 እነርሱ ብቻ ወደ መቅደሴ ይገባሉ፤ እነርሱ ብቻ በፊቴ ሊያገለግሉ፣ ሥርዐቴንም ሊፈጽሙና ወደ ገበታዬ ሊቀርቡ ይችላሉ።
17 ‘ “ወደ ውስጠኛው አደባባይ በሮች ሲገቡ፣ የበፍታ ፈትል ይልበሱ፤ በውስጠኛው አደባባይ በሮችም ሆነ በቤተ መቅደሱ ውስጥ ሲያገለግሉ፣ ከበግ ጠጒር የተሠራ ልብስ አይልበሱ።
18 በራሳቸው ላይ ከበፍታ ፈትል የተሠራ ጥምጥም ያድርጉ፤ እንዲሁም ከበፍታ ፈትል የተሠራ ሱሪ በወገባቸው ላይ ይታጠቁ፤ እንዲያልባቸው የሚያደርግ ማንኛውንም ልብስ አይልበሱ።
19 ሕዝቡ ወዳለበት ወደ ውጩ አደባባይ ሲወጡ፣ ሲያገለግሉበት የነበረውን ልብስ አውልቀው በተቀደሱት ክፍሎች በመተው ሌሎች ልብሶችን ይልበሱ፤ ይኸውም ሕዝቡን በልብሳቸው እንዳይቀድሱ ነው።