ሕዝቅኤል 44:16-22 NASV

16 እነርሱ ብቻ ወደ መቅደሴ ይገባሉ፤ እነርሱ ብቻ በፊቴ ሊያገለግሉ፣ ሥርዐቴንም ሊፈጽሙና ወደ ገበታዬ ሊቀርቡ ይችላሉ።

17 ‘ “ወደ ውስጠኛው አደባባይ በሮች ሲገቡ፣ የበፍታ ፈትል ይልበሱ፤ በውስጠኛው አደባባይ በሮችም ሆነ በቤተ መቅደሱ ውስጥ ሲያገለግሉ፣ ከበግ ጠጒር የተሠራ ልብስ አይልበሱ።

18 በራሳቸው ላይ ከበፍታ ፈትል የተሠራ ጥምጥም ያድርጉ፤ እንዲሁም ከበፍታ ፈትል የተሠራ ሱሪ በወገባቸው ላይ ይታጠቁ፤ እንዲያልባቸው የሚያደርግ ማንኛውንም ልብስ አይልበሱ።

19 ሕዝቡ ወዳለበት ወደ ውጩ አደባባይ ሲወጡ፣ ሲያገለግሉበት የነበረውን ልብስ አውልቀው በተቀደሱት ክፍሎች በመተው ሌሎች ልብሶችን ይልበሱ፤ ይኸውም ሕዝቡን በልብሳቸው እንዳይቀድሱ ነው።

20 ‘ “የራሳቸውን ጠጒር አይላጩት፤ ወይም አያርዝሙት፤ ነገር ግን ይከርክሙት።

21 ማንኛውም ካህን ወደ ውስጠኛው አደባባይ በሚገባበት ጊዜ የወይን ጠጅ አይጠጣ።

22 መበለቶችን ወይም ፈት ሴቶችን አያግቡ፤ ነገር ግን ከእስራኤል ዘር የሆኑ ድንግሎችን ወይም የካህናት ሚስቶች የነበሩትን መበለቶች ማግባት ይችላሉ።