ሕዝቅኤል 44:4-10 NASV

4 ከዚያም ያ ሰው በሰሜኑ በር በኩል ወደ ቤተ መቅደሱ ፊት ለፊት አመጣኝ፤ እኔም ተመለከትሁ፤ የእግዚአብሔርም ክብር የእግዚአብሔርን ቤተ መቅደስ ሞልቶት አየሁ፤ በግንባሬም ተደፋሁ።

5 እግዚአብሔር እንዲህ አለኝ፤ “የሰው ልጅ ሆይ፤ ስለ እግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ሥርዐት የምነግርህን ሁሉ በጥንቃቄ አስተውል፤ በሚገባ አድምጥ፤ ልብም በለው። የቤተ መቅደሱን መግቢያና የመቅደሱን መውጫዎች ሁሉ አስተውል፤

6 ለዐመፀኛው የእስራኤል ቤት እንዲህ በል፤ ‘ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ “የእስራኤል ቤት ሆይ፤ አስጸያፊ ሥራችሁ ከእንግዲህ ያብቃ!

7 ከአስጸያፊ ሥራችሁም ሌላ ምግብ፣ ስብና ደም ስታቀርቡ ልባቸውንና ሥጋቸውን ያልተገረዙትን እንግዶች ወደ መቅደሴ በማስገባት ቤተ መቅደሴን አረከሳችሁ፤ ቃል ኪዳኔንም አፈረሳችሁ።

8 እናንተ ራሳችሁ ማድረግ የሚገባችሁን ቅዱሳት ሥርዐቶቼን በመፈጸም ፈንታ ባዕዳንን በኀላፊነት በመቅደሴ አስቀመጣችሁ።

9 ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ በልቡና በሥጋው ያልተገረዘ ባዕድ በእስራኤላውያን መካከል የሚኖር ቢሆንም እንኳ ወደ መቅደሴ አይግባ።

10 ‘ “እስራኤል እኔን ከመከተል በራቁ ጊዜ፣ ከእኔ የራቁትና ጣዖቶቻቸውን በመከተል የተቅበዘበዙት ሌዋውያን የኀጢአታቸውን ዕዳ ይሸከማሉ።