ሕዝቅኤል 45:10-16 NASV

10 ትክክለኛ ሚዛን ትክክለኛ ኢፍና ትክክለኛ ባዶስ ይኑራችሁ።

11 የኢፍና የባዶሱ መመዘኛ ተመሳሳይ ይሁን፤ አንድ ባዶስ የሆመር አንድ ዐሥረኛ እንዲሁም አንድ ኢፍ የሆመር አንድ ዐሥረኛ ይሆናል፤ ሆመር ለሁለቱም ሚዛኖች መደበኛ መለኪያ ነው።

12 አንድ ሰቅል ሃያ ጌራህ የሚይዝ ይሆናል፤ በሃያ ሰቅል ላይ ሃያ አምስት ሰቅልና ዐሥራ አምስት ሰቅል ሲጨመር አንድ ምናን ይሆናል።’

13 ‘ “የምታቀርቡት ልዩ መባ ይህ ነው፤ ከአንድ ሆመር መስፈሪያ ስንዴ አንድ ስድስተኛ ኢፍ እንዲሁም ከእያንዳንዱ ሆመር ገብስ አንድ ስድስተኛ ኢፍ ነው።

14 ዘይቱ በባዶስ ሲለካ የተወሰነው መስፈሪያ ከእያንዳንዱ ሆመር አንድ ዐሥረኛ ባዶስ ይሆናል፤ ይኸውም ዐሥር ባዶስ ወይም አንድ ሆመር ነው፤ ዐሥር ባዶስ ከአንድ ሆመር ጋር እኩል ነውና።

15 እንዲሁም ውሃ ከጠገበው ከእስራኤል መሰማሪያ፣ ሁለት መቶ በግ ካለው ከእያንዳንዱ መንጋ አንድ በግ ይውሰድ። ይህ ሁሉ ለሕዝቡ ማስተስረያ ለሚሆነው ለእህል ቍርባን፣ ለሚቃጠል መሥዋዕትና ለኅብረት መሥዋዕት ይውላል፤ ይላል ጌታ እግዚአብሔር።

16 የምድሪቱ ሕዝብ ሁሉ ይህን ልዩ መባ ለእስራኤል ገዥ ይሰጣሉ።