ሕዝቅኤል 46:3-9 NASV

3 የምድሪቱም ሕዝብ በሰንበታትና በወር መባቻ በዓላት በእግዚአብሔር ፊት በበሩ መግቢያ ላይ ይስገዱ።

4 ገዡ በሰንበት ቀን በእግዚአብሔር ፊት የሚያቀርበው የሚቃጠል መሥዋዕት ስድስት የበግ ጠቦትና አንድ አውራ በግ ነው፤ ሁሉም እንከን የሌላቸው ይሁኑ።

5 ከአውራ በጉ ጋር የሚቀርበው የእህል ቍርባን አንድ የኢፍ መስፈሪያ ይሁን፤ ከበግ ጠቦቶቹ ጋር የሚቀርበውም የእህል ቍርባን ሰውየው የወደደውን ያህል ይሁን፤ እያንዳንዱም የኢፍ መስፈሪያ አንድ የኢን መስፈሪያ ዘይት ይኑረው።

6 በወር መባቻ በዓል አንድ ወይፈን፣ ስድስት የበግ ጠቦትና አንድ አውራ በግ ያቅርብ፤ ሁሉም እንከን የሌለባቸው ይሁኑ።

7 ከወይፈኑ ጋር አንድ የኢፍ መስፈሪያ፣ ከአውራው በግም ጋር አንድ የኢፍ መስፈሪያ የእህል ቍርባን ያቅርብ፤ ከበግ ጠቦቶቹ ጋር የሚቀርበው የእህል ቍርባን ደግሞ ሰውየው የወደደውን ያህል ይሁን፤ እያንዳንዱም የኢፍ መስፈሪያ የኢን መስፈሪያ ዘይት ይኑረው።

8 ገዡ ሲገባ፣ በመግቢያው በር መተላለፊያ በረንዳ ይግባ፤ ሲወጣም በዚያው ይውጣ።

9 “ ‘በተወሰኑት በዓላት የምድሪቱ ሕዝብ በእግዚአብሔር ፊት በሚቀርብበት ጊዜ፣ ይሰግድ ዘንድ በሰሜን በር የገባ ሁሉ በደቡብ በር ይውጣ፤ በደቡብ በር የገባም በሰሜኑ በር ይውጣ፤ በፊት ለፊቱ ባለው በር ይመለስ እንጂ ማንም በገባበት በር አይውጣ።