ሕዝቅኤል 46:6-12 NASV

6 በወር መባቻ በዓል አንድ ወይፈን፣ ስድስት የበግ ጠቦትና አንድ አውራ በግ ያቅርብ፤ ሁሉም እንከን የሌለባቸው ይሁኑ።

7 ከወይፈኑ ጋር አንድ የኢፍ መስፈሪያ፣ ከአውራው በግም ጋር አንድ የኢፍ መስፈሪያ የእህል ቍርባን ያቅርብ፤ ከበግ ጠቦቶቹ ጋር የሚቀርበው የእህል ቍርባን ደግሞ ሰውየው የወደደውን ያህል ይሁን፤ እያንዳንዱም የኢፍ መስፈሪያ የኢን መስፈሪያ ዘይት ይኑረው።

8 ገዡ ሲገባ፣ በመግቢያው በር መተላለፊያ በረንዳ ይግባ፤ ሲወጣም በዚያው ይውጣ።

9 “ ‘በተወሰኑት በዓላት የምድሪቱ ሕዝብ በእግዚአብሔር ፊት በሚቀርብበት ጊዜ፣ ይሰግድ ዘንድ በሰሜን በር የገባ ሁሉ በደቡብ በር ይውጣ፤ በደቡብ በር የገባም በሰሜኑ በር ይውጣ፤ በፊት ለፊቱ ባለው በር ይመለስ እንጂ ማንም በገባበት በር አይውጣ።

10 ገዡ በመካከላቸው በመሆን፣ ሲገቡ ይገባል፤ ሲወጡም ይወጣል።

11 “ ‘በበዓላትና በተወሰኑት በዓላት፣ ከወይፈኑ ጋር አንድ የኢፍ መስፈሪያ፣ ከአውራ በጉም ጋር አንድ የኢፍ መስፈሪያ የእህል ቍርባን ያቅርብ፤ ከበግ ጠቦቶቹ ጋር የሚያቀርበው የእህል ቍርባን ግን ሰውየው የወደደውን ያህል ይሁን፤ እያንዳንዱም የኢፍ መስፈሪያ አንድ የኢን መስፈሪያ ዘይት ይኑረው።

12 ገዡ በፈቃዱ ለእግዚአብሔር የሚቃጠል መሥዋዕትም ሆነ የኅብረት መሥዋዕት በሚያቀርብበት ጊዜ፣ በምሥራቅ ትይዩ የሆነው በር ይከፈትለት፤ በሰንበት ቀን እንደሚያደርገው ሁሉ የሚቃጠል መሥዋዕቱንም ሆነ የኅብረት መሥዋዕቱን ያቅርብ፤ ከዚያ በኋላ ይወጣል፤ በሩም ይዘጋል።