ሕዝቅኤል 48:11-17 NASV

11 ይህም እስራኤላውያን በሳቱ ጊዜ፣ እንደ ሳቱት ሌዋውያን ሳይስቱ ለቀሩት፣ በታማኝነት ላገለገሉኝ ለተቀደሱት ካህናት ለሳዶቃውያን ይሆናል።

12 የሌዋውያንን ምድር ከሚያዋስነው፣ ከምድሪቱ ቅዱስ ድርሻ እጅግ የተቀደሰው ድርሻ ለእነርሱ ልዩ ስጦታ ይሆናል።

13 “ከካህናቱም ምድር ጐን ለጐን ሌዋውያኑ ሃያ አምስት ሺህ ክንድ ርዝመትና ዐሥር ሺህ ክንድ ወርድ ያለው ይዞታ ይኖራቸዋል፤ ጠቅላላ ርዝመቱ ሃያ አምስት ሺህ ክንድ፣ ወርዱም ዐሥር ሺህ ክንድ ይሆናል።

14 ከዚህ ላይ መሸጥ ወይም መለወጥ የለባቸውም። ይህ ከምድሪቱ ሁሉ ምርጥ ስለ ሆነ፣ ወደ ሌላ እጅ አይተላለፍም፤ ለእግዚአብሔር የተቀደሰ ነውና።

15 “አምስት ሺህ ክንድ ወርድና ሃያ አምስት ሺህ ክንድ ርዝመት ያለው የቀረው ቦታ ለከተማዪቱ የጋራ ጥቅም፣ ለቤት ሥራና ለከብት ማሰማሪያ ይውላል፤ ከተማዪቱም በመካከሉ ትሆናለች፤

16 የከተማዪቱም መጠን በሰሜን አራት ሺህ አምስት መቶ ክንድ፣ በደቡብ አራት ሺህ አምስት መቶ ክንድ፣ በምሥራቅ አራት ሺህ አምስት መቶ ክንድ፣ የምዕራቡም እንዲሁ አራት ሺህ አምስት መቶ ክንድ ይሆናል።

17 የከተማዪቱ ከብት ማሰማሪያ ቦታ፣ በሰሜን ሁለት መቶ አምሳ ክንድ፣ በደቡብ ሁለት መቶ አምሳ ክንድ፣ በምሥራቅ ሁለት መቶ አምሳ ክንድ፣ በምዕራብም ሁለት መቶ አምሳ ክንድ ይሆናል።