ሕዝቅኤል 6:2-8 NASV

2 “የሰው ልጅ ሆይ፤ ፊትህን ወደ እስራኤል ተራሮች አዙር፤ ትንቢትም ተናገርባቸው፤

3 እንዲህም በል፤ ‘የእስራኤል ተራሮች ሆይ፤ የጌታ የእግዚአብሔርን ቃል ስሙ፤ ጌታ እግዚአብሔር ለተራሮችና ለኰረብቶች፤ ለገደላገደሎችና ለሸለቆች እንዲህ ይላል፤ “ሰይፍን አመጣባችኋለሁ፤ የማምለኪያ ኰረብቶቻችሁን አጠፋለሁ።

4 መሠዊያዎቻችሁ ይፈርሳሉ፤ የዕጣን መሠዊያዎቻችሁም ይሰባበራሉ፤ የታረዱ ሰዎቻችሁን በጣዖቶቻችሁ ፊት እጥላለሁ።

5 የእስራኤላውያንን ሬሳ በጣዖቶቻችሁ ፊት አጋድማለሁ፤ ዐጥንቶቻችሁንም በመሠዊያዎቻችሁ ዙሪያ እበትናለሁ።

6 መሠዊያዎቻችሁ እንዲፈራርሱና እንዲወድሙ፣ ጣዖቶቻችሁ እንዲሰባበሩና እንዲደቁ፣ የዕጣን መሠዊያዎቻችሁ እንዲንኰታኰቱ፣ የእጆቻችሁም ሥራ እንዲደመሰስ፣ የምትኖሩባቸው ከተሞች ሁሉ ባድማ ይሆናሉ፤ ማምለኪያ ኰረብቶችም እንዳልነበሩ ይሆናሉ።

7 የታረዱ ሰዎቻችሁ በመካከላችሁ ይወድቃሉ፤ እኔም እግዚአብሔር እንደሆንሁ ታውቃላችሁ።”

8 “በአሕዛብ መካከል ስትበተኑ፣ አንዳንዶቻችሁ ከሰይፍ ታመልጣላችሁና፣ ጥቂት ሰዎችን አስቀራለሁ።