ሕዝቅኤል 6:5-11 NASV

5 የእስራኤላውያንን ሬሳ በጣዖቶቻችሁ ፊት አጋድማለሁ፤ ዐጥንቶቻችሁንም በመሠዊያዎቻችሁ ዙሪያ እበትናለሁ።

6 መሠዊያዎቻችሁ እንዲፈራርሱና እንዲወድሙ፣ ጣዖቶቻችሁ እንዲሰባበሩና እንዲደቁ፣ የዕጣን መሠዊያዎቻችሁ እንዲንኰታኰቱ፣ የእጆቻችሁም ሥራ እንዲደመሰስ፣ የምትኖሩባቸው ከተሞች ሁሉ ባድማ ይሆናሉ፤ ማምለኪያ ኰረብቶችም እንዳልነበሩ ይሆናሉ።

7 የታረዱ ሰዎቻችሁ በመካከላችሁ ይወድቃሉ፤ እኔም እግዚአብሔር እንደሆንሁ ታውቃላችሁ።”

8 “በአሕዛብ መካከል ስትበተኑ፣ አንዳንዶቻችሁ ከሰይፍ ታመልጣላችሁና፣ ጥቂት ሰዎችን አስቀራለሁ።

9 እነዚህ ከሰይፍ የተረፉት፣ ከእኔ ዘወር ባለ አመንዝራ ልባቸውና ጣዖትን በተከተለ አመንዝራ ዐይናቸው የቱን ያህል እንዳሳዘኑኝ፤ በአሕዛብ ምድር ሆነው ያስታውሱኛል፤ ካደረጉት ክፋትና ከፈጸሙት ርኩስ ተግባር ሁሉ የተነሣም ራሳቸውን ይጸየፋሉ።

10 እነርሱም እኔ እግዚአብሔር እንደሆንሁ ያውቃሉ፤ ይህንም ክፉ ነገር አመጣባቸዋለሁ ብዬ የተናገርሁት በከንቱ አይደለም።

11 “ ‘ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ “የእስራኤል ቤት ካደረጉት ክፋትና ከፈጸሙት ጸያፍ ተግባራቸው ሁሉ የተነሣ በሰይፍ በራብና በቸነፈር ይወድቃሉና፤ በእጅህ እያጨበጨብህ በእግርህም መሬት እየረገጥህ፣ ‘ወየው!’ ብለህ ጩኽ።