ሕዝቅኤል 8:1-7 NASV

1 በስድስተኛው ዓመት፣ በስድስተኛው ወር፣ በአምስተኛው ቀን በቤቴ ተቀምጬ ሳለሁ፣ የይሁዳም ሽማግሌዎች በፊቴ ተቀምጠው ሳሉ፣ በዚያ የጌታ እግዚአብሔር እጅ በላዬ መጣች።

2 እኔም አየሁ፤ እነሆ፤ የሰውን ልጅ የሚመስል ነበረ፤ ወገቡ ከሚመስለው ጀምሮ ወደ ታች እንደ እሳት ያለ ነበር፤ ወገቡንም ከሚመስለው ጀምሮ ወደ ላይ እንደ ጋለ ብረት ያበራ ነበር።

3 እርሱም እጅ መሳይ ዘርግቶ የራስ ጠጒሬን ያዘ፤ መንፈስም በምድርና በሰማይ መካከል አነሣኝ፤ እርሱም ቅናት የሚያነሣው ጣዖት ወደ ቆመበት፣ ወደ ውስጠኛው አደባባይ መግቢያ ወደ ሰሜን በር ወደ ኢየሩሳሌም በእግዚአብሔር ራእይ ወሰደኝ።

4 እነሆ፤ በረባዳው ስፍራ በራእይ ያየሁት የእስራኤል አምላክ ክብር በዚያ ነበረ።

5 እርሱም፣ “የሰው ልጅ ሆይ፤ ወደ ሰሜን ተመልከት” አለኝ። እኔም ተመለከትሁ፤ እነሆ ከመሠዊያው በር በሰሜን በኩል መግቢያው ላይ ይህ የቅናት ጣዖት ነበረ።

6 ደግሞም፣ “የሰው ልጅ ሆይ፤ የእስራኤል ቤት ከመቅደሴ ያርቀኝ ዘንድ በዚህ የሚያደርገውን እጅግ አስጸያፊ ነገር ታያለህን? ከዚህም የባሰ አስጸያፊ ነገር ታያለህ” አለኝ።

7 ከዚያም በኋላ ወደ አደባባዩ መግቢያ አመጣኝ፤ እኔም ግንቡን ተመለከትሁ፤ ቀዳዳም ነበረበት።