ሕዝቅኤል 8:5-11 NASV

5 እርሱም፣ “የሰው ልጅ ሆይ፤ ወደ ሰሜን ተመልከት” አለኝ። እኔም ተመለከትሁ፤ እነሆ ከመሠዊያው በር በሰሜን በኩል መግቢያው ላይ ይህ የቅናት ጣዖት ነበረ።

6 ደግሞም፣ “የሰው ልጅ ሆይ፤ የእስራኤል ቤት ከመቅደሴ ያርቀኝ ዘንድ በዚህ የሚያደርገውን እጅግ አስጸያፊ ነገር ታያለህን? ከዚህም የባሰ አስጸያፊ ነገር ታያለህ” አለኝ።

7 ከዚያም በኋላ ወደ አደባባዩ መግቢያ አመጣኝ፤ እኔም ግንቡን ተመለከትሁ፤ ቀዳዳም ነበረበት።

8 እርሱም፣ “የሰው ልጅ ሆይ፤ ግንቡን ንደለው” አለኝ፤ እኔም ግንቡን ነደልሁት፤ አንድ በርም አገኘሁ።

9 እርሱም፣ “ግባና በዚህ የሚፈጽሙትን እጅግ የከፋ ርኵሰት ተመልከት አለኝ።

10 እኔም ገብቼ አየሁ፤ እነሆ በደረታቸው የሚሳቡ ፍጡራንና የርኵሳን አራዊት ዐይነት ሁሉ፣ የእስራኤልም ቤት ጣዖታት ሁሉ ዙሪያውን በግንቡ ላይ ተቀርጸው ነበር።

11 በእነዚህም ፊት ከእስራኤል ቤት ሰባ ሽማግሌዎች ቆመው ነበር፤ በመካከላቸውም የሳፋን ልጅ ያእዛንያ ቆሞ ነበር፤ እያንዳንዳቸውም በእጃቸው ጥና ይዘዋል፤ መልካም መዐዛ ያለው የዕጣን ጢስም እየተትጐለጐለ ይወጣ ነበር።