ኢሳይያስ 29:4-10 NASV

4 ወደ ታች ትወርጃለሽ፤ ከምድርም በታች ትናገሪያለሽ፤ንግግርሽ ከትቢያ እየተጒተመተመ ይወጣል፤ድምፅሽ እንደ መናፍስት ድምፅ ከመሬት ወደ ላይ ይመጣል፤ንግግርሽ ከትቢያ ያንሾካሹካል።

5 ነገር ግን ብዙ ጠላቶችሽ እንደ ትቢያ ብናኝ፣መንጋ ጨካኞችም በነፋስ እንደሚነጻገለባ ይሆናሉ።ድንገት ሳይታሰብም፣

6 የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር፣በነጐድጓድ፣ በምድር መናወጥና በታላቅ ድምፅ፣በዐውሎ ነፋስና በኀይለኛ ሞገድ ፈጽሞ በሚባላም የእሳት ነበልባል ይመጣል።

7 አርኤልን የሚወጋ የአሕዛብ ሁሉ መንጋ፣በእርሷና በምሽጓ ላይ አደጋ የሚጥልና የሚከባት፣እንደ ሕልምበሌሊትም እንደሚታይ ራእይ ይሆናል።

8 የተራበ ሰው በሕልሙ ሲበላ ዐድሮ፣ነገር ግን ሲነቃ ራቡ እንዳልለቀቀው፣የጠማውም ሰው በሕልሙ ሲጠጣ ዐድሮ፣ነገር ግን ሲነቃ እንደ ዛለና ጥማቱም እንዳልተወው፣የጽዮንን ተራራ የሚወጋ፣የአሕዛብ መንጋ ሁሉ እንዲሁ ይሆናል።

9 ነሁሉሉ፤ ተደነቁም፤ተጨፈኑ፤ እስከ ወዲያኛውም ታውራችሁ ቅሩ፤በወይን ጠጅ አይሁን እንጂ ስከሩ፤በሚያሰክር መጠጥ አይሁን እንጂ ተንገዳገዱ።

10 እግዚአብሔር ከባድ እንቅልፍ ጥሎባችኋል፤ዐይኖቻችሁን፣ ነቢያትን ጨፍኖባችኋል፤ራሶቻችሁን፣ ባለ ራእዮችን ሸፍኖባችኋል።