ኢሳይያስ 65:15-21 NASV

15 ስማችሁንም፣የተመረጠው ሕዝቤ ርግማን እንዲያደርገው ትተዋላችሁ፤ጌታ እግዚአብሔር ይገድላችኋል፤ለአገልጋዮቹ ግን ሌላ ስም ይሰጣቸዋል።

16 ስለዚህ በምድሪቱ ላይ በረከትን የሚጠራ፣በእውነት አምላክ ስም ይባረካል፤በምድሪቱ መሐላን የሚምል፣በእውነት አምላክ ስም ይምላል፤ያለፉት ችግሮች ተረስተዋል፤ከዐይኖቼም ተሰውረዋል።

17 “እነሆ፤ እኔ፣አዲስ ሰማያትንና አዲስ ምድርን እፈጥራለሁ፤ያለፉት ነገሮች አይታሰቡም፤አይታወሱም።

18 ነገር ግን በምፈጥረው፣ደስ ይበላችሁ፤ ለዘላለም ሐሤት አድርጉ።ኢየሩሳሌምን ለደስታ፣ሕዝቧን ለሐሤት እፈጥራለሁና።

19 በኢየሩሳሌም እደሰታለሁ፤በሕዝቤ ሐሤት አደርጋለሁ፤የልቅሶና የጩኸት ድምፅ፣ከእንግዲህ በዚያ አይሰማም።

20 “ከእንግዲህም በዚያ፣ለጥቂት ጊዜ ብቻ በሕይወት የሚኖር ሕፃን፣ወይም ዕድሜ ያልጠገበ አረጋዊ አይኖርም፤አንድ መቶ ዓመት የሞላው ሰው ቢሞት፣በአጭር እንደ ተቀጨ ይቈጠራል፤አንድ ሰው መቶ ዓመት ሳይሞላው ቢሞት፣እንደ ተቀሠፈ ይገመታል።

21 ሰዎች ቤት ይሠራሉ፤ በውስጡም ይኖራሉ፤ወይንን ይተክላሉ፤ ፍሬውንም ይበላሉ።