ኤርምያስ 1:13-19 NASV

13 ዳግመኛም የእግዚአብሔር ቃል፣ “ምን ታያለህ?” ሲል ወደ እኔ መጣ።እኔም፣ “አንድ የሚፈላ ማሰሮ አያለሁ፤ አፉም ከሰሜን ወደዚህ ያዘነበለ ነው” አልሁ።

14 እግዚአብሔርም እንዲህ አለኝ፤ “ከሰሜን በምድሪቱ በሚኖሩ ሁሉ ላይ ድንገት መዓት ይወርድባቸዋል።

15 እነሆ፤ የሰሜን መንግሥታትን ሕዝቦች ሁሉ እጠራለሁ” ይላል እግዚአብሔር፤“ንጉሦቻቸው ይመጣሉ፤ዙፋናቸውን በኢየሩሳሌም መግቢያ በሮች፣በቅጥሮቿ ዙሪያ ሁሉ፣በይሁዳም ከተሞች ሁሉ ይዘረጋሉ።

16 እኔን በመተው ክፋት ስለ ሠሩ፣ለሌሎች አማልክት ዕጣን ስላጠኑ፣እጆቻቸው የሠሯቸውን ስላመለኩ፣በሕዝቤ ላይ ፍርድን ዐውጄአለሁ።

17 “አንተ ግን ወገብህን ታጠቅ፤ ተነሥተህም ያዘዝሁን ሁሉ ንገራቸው፤ አትፍራቸውም፤ አለዚያ በፊታቸው አስፈራሃለሁ።

18 እነሆ፤ ዛሬ በመላዪቱ ምድር ላይ አስነሣሃለሁ ይኸውም የይሁዳን ነገሥታት፣ አለቆቿን፣ ካህናቷንና የምድሪቱን ሕዝብ ሁሉ መቋቋም እንድትችል የተመሸገ ከተማ፣ የብረት ምሰሶና የናስ ቅጥር አድርጌሃለሁ።

19 ይዋጉሃል፤ ዳሩ ግን አድንህ ዘንድ እኔ ከአንተ ጋር ነኝና አያሸንፉህም” ይላል እግዚአብሔር።