ኤርምያስ 15:4-10 NASV

4 የይሁዳ ንጉሥ የሕዝቅያስ ልጅ ምናሴ በኢየሩሳሌም ካደረገው በደል የተነሣ፣ ለምድር ነገሥታት ሁሉ መሰቀቂያ አደርጋቸዋለሁ።

5 “ኢየሩሳሌም ሆይ፤ የሚራራልሽ ማን ነው?ማንስ ያለቅስልሻል?ደኅንነትሽንስ ማን ጎራ ብሎ ይጠይቃል?

6 እኔን ጥለሽኛል” ይላል እግዚአብሔር፤“ወደ ኋላም እያፈገፈግሽ ነው፤ስለዚህ እጄን በአንቺ ላይ አነሣለሁ፤ አጠፋሻለሁም፤ከእንግዲህም አልራራልሽም።

7 በአገሪቱ የከተማ ደጆች፣በመንሽ እበትናቸዋለሁ፤ከመንገዳቸው አልተመለሱምና፣ሕዝቤን በሐዘን እመታለሁ፤ጥፋትም አመጣባቸዋለሁ፤

8 የመበለቶቻቸውን ቍጥር፣ከባሕር አሸዋ ይልቅ አበዛለሁ፤የጐበዛዝት እናቶች በሆኑትም ላይ፣አጥፊውን በቀትር አመጣባቸዋለሁ።ሽብርንና ድንጋጤን፣በድንገት አወርድባቸዋለሁ።

9 የሰባቶቹ እናት ትዝለፈለፋለች፤ትንፋሿም ይጠፋል፤ገና ቀን ሳለ ፀሓይዋ ትጠልቃለች፤እርሷም ታፍራለች፤ ትዋረዳለችም፤የተረፉትንም በጠላቶቻቸው ፊት፣ለሰይፍ እዳርጋቸዋለሁ፤”ይላል እግዚአብሔር።

10 ወይኔ እናቴ! ለምድር ሁሉ፣የጭቅጭቅና የክርክር ሰው የሆንሁትን ምነው ወለድሽ!ለማንም አላበደርሁም፤ ከማንም አልተበደርሁም፤ነገር ግን ሰው ሁሉ ይረግመኛል።