ኤርምያስ 15:6-12 NASV

6 እኔን ጥለሽኛል” ይላል እግዚአብሔር፤“ወደ ኋላም እያፈገፈግሽ ነው፤ስለዚህ እጄን በአንቺ ላይ አነሣለሁ፤ አጠፋሻለሁም፤ከእንግዲህም አልራራልሽም።

7 በአገሪቱ የከተማ ደጆች፣በመንሽ እበትናቸዋለሁ፤ከመንገዳቸው አልተመለሱምና፣ሕዝቤን በሐዘን እመታለሁ፤ጥፋትም አመጣባቸዋለሁ፤

8 የመበለቶቻቸውን ቍጥር፣ከባሕር አሸዋ ይልቅ አበዛለሁ፤የጐበዛዝት እናቶች በሆኑትም ላይ፣አጥፊውን በቀትር አመጣባቸዋለሁ።ሽብርንና ድንጋጤን፣በድንገት አወርድባቸዋለሁ።

9 የሰባቶቹ እናት ትዝለፈለፋለች፤ትንፋሿም ይጠፋል፤ገና ቀን ሳለ ፀሓይዋ ትጠልቃለች፤እርሷም ታፍራለች፤ ትዋረዳለችም፤የተረፉትንም በጠላቶቻቸው ፊት፣ለሰይፍ እዳርጋቸዋለሁ፤”ይላል እግዚአብሔር።

10 ወይኔ እናቴ! ለምድር ሁሉ፣የጭቅጭቅና የክርክር ሰው የሆንሁትን ምነው ወለድሽ!ለማንም አላበደርሁም፤ ከማንም አልተበደርሁም፤ነገር ግን ሰው ሁሉ ይረግመኛል።

11 እግዚአብሔር እንዲህ አለ፤“በእርግጥ ለበጎ ዐላማ እታደግሃለሁ፤በመከራና በጭንቅ ጊዜም፣ጠላቶችህ ደጅ እንዲጠኑህ በእውነት አደርጋለሁ።

12 “ሰው ብረትን፣ ከሰሜን የመጣን ብረት፣ነሐስንስ መስበር ይችላልን?