ኤርምያስ 17:21-27 NASV

21 እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ “በሰንበት ቀን ሸክም ተሸክማችሁ በኢየሩሳሌም በሮች እንዳታስገቡ ለራሳችሁ ተጠንቀቁ።

22 አባቶቻችሁን እንዳዘዝኋቸው ሰንበትን አክብሩ እንጂ በሰንበት ቀን ከየቤታችሁ ሸክም ይዛችሁ አትውጡ፤ ምንም ሥራ አትሥሩ።”

23 እነርሱ ግን አልሰሙም፤ ልብም አላሉም፤ እንዳይሰሙና እንዳይገሠጹም ዐንገታቸውን አደነደኑ።

24 ነገር ግን በጥንቃቄ ብት ታዘዙኝ ይላል እግዚአብሔር፤ በሰንበትም ቀን በዚህች ከተማ በሮች ሸክም ይዛችሁ ባትገቡ፣ የሰንበትንም ቀን ምንም ሳትሠሩ ብትቀድሱት፣

25 በዳዊት ዙፋን ላይ የሚቀመጡ ነገሥታትና መኳንንታቸው በዚህች ከተማ በሮች ይገባሉ፤ በፈረሶችና በሠረገሎች ተቀምጠው በይሁዳ ሰዎችና በኢየሩሳሌም ነዋሪዎች ታጅበው ይመጣሉ፤ ይህቺም ከተማ ለዘላለም የሰው መኖሪያ ትሆናለች።

26 ሰዎች ከይሁዳ ከተሞች፣ ከኢየሩሳሌም ዙሪያ፣ ከብንያምም አገር፣ ከቈላውና ከደጋው አገር እንዲሁም ከኔጌቭ የሚቃጠል መሥዋዕትና ሌላ መሥዋዕት፣ የእህል ቍርባን፣ ዕጣንና የምስጋና መሥዋዕት ይዘው ወደ እግዚአብሔር ቤት ይመጣሉ።

27 ነገር ግን የሰንበትን ቀን ሳትቀድሱ፣ በሰንበት ቀን ሸክም ተሸክማችሁ በኢየሩሳሌም በሮች በመግባት ትእዛዜን ብትጥሱ፣ በኢየሩሳሌም በሮች ላይ ምሽጎቿን የሚበላ፣ የማይጠፋ እሳት እጭራለሁ።”