ኤርምያስ 19:1-6 NASV

1 እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ “ሄደህ፣ ከሸክላ ሠሪ ገምቦ ግዛ፤ ከሕዝቡና ከካህናቱ መካከል ታላላቅ የሆኑትን አንዳንዶቹን ይዘህ፣

2 በገል በር መግቢያ አጠገብ ወዳለው ወደ ሄኖም ልጅ ሸለቆ ውጣ። በዚያም የምነግርህን ቃል ተናገር፤

3 እንዲህም በል፤ ‘የይሁዳ ነገሥታትና በኢየሩሳሌም የምትኖሩ ሆይ፤ የእግዚአብሔርን ቃል ስሙ፤ የእስራኤል አምላክ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ “ለሰሚው ሁሉ ጆሮ የሚዘገንን ክፉ ነገር እነሆ በዚህ ስፍራ አመጣለሁ፤

4 እኔን ትተውኝ፣ ይህን ስፍራ የባዕድ አማልክት ቦታ አድርገውታልና። እነርሱም ሆኑ አባቶቻቸው፣ የይሁዳ ነገሥታትም ለማያውቋቸው አማልክት ሠውተዋል፤ ይህንም ስፍራ በንጹሓን ደም ሞልተውታል፤

5 እኔም ያላዘዝኋቸውን፣ ያልተናገርኋቸውን፣ ፈጽሞም ያላሰብሁትን፣ ወንዶች ልጆቻቸውን በእሳት ሊሠውለት ለበኣል መስገጃ ኰረብታዎች ሠርተዋል።

6 ስለዚህ ሰዎች ይህን ስፍራ የዕርድ ሸለቆ እንጂ ከእንግዲህ ቶፌት ወይም የሄኖም ልጅ ሸለቆ ብለው የማይጠሩበት ዘመን ይመጣል፤ ይላል እግዚአብሔር።