1 በእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ውስጥ አለቃ የነበረው፣ የኢሜር ልጅ ካህኑ ጳስኮር እነዚህን ነገሮች ኤርምያስ እንደ ተነበየ በሰማ ጊዜ፣
2 ነቢዩ ኤርምያስን መታው፣ በእግዚአብሔርም ቤተ መቅደስ በላይኛው የብንያም በር በእግር ግንድ ጠረቀው።
3 በማግስቱም ጳስኮር ኤርምያስን ከተጠረቀበት ግንድ አወጣው፤ ኤርምያስም እንዲህ አለው፤ “እግዚአብሔር ከእንግዲህ ማጎርሚሳቢብ ብሎ ይጠራሃል እንጂ ጳስኮር አይልህም፤
4 እግዚአብሔር እንዲህ ይላልና፤ ‘አንተንና ባልንጀሮችህን ሁሉ ለሽብር እዳርጋለሁ፤ የገዛ ዐይንህ እያየ በጠላቶቻቸው ሰይፍ ይወድቃሉ። ይሁዳን ሁሉ ለባቢሎን ንጉሥ አሳልፌ እሰጣለሁ፤ እርሱም ወደ ባቢሎን ያፈልሳቸዋል፤ በሰይፍም ይገድላቸዋል።
5 የዚህችን ከተማ ሀብት ሁሉ፣ ጥሪቷን፣ የይሁዳን ነገሥታት ውድ ዕቃና ንብረት ሁሉ ለጠላቶቻቸው አሳልፌ እሰጣለሁ፤ እነርሱም ዘርፈው ወደ ባቢሎን ይዘውት ይሄዳሉ።