ኤርምያስ 23:5-11 NASV

5 “እነሆ፤ ለዳዊት፣ጻድቅ ቅርንጫፍ የማስነሣበት ጊዜ ይመጣል፤እርሱም ፍትሕንና ጽድቅን የሚያደርግ፣በጥበብ የሚገዛ ንጉሥ ይሆናል” ይላል እግዚአብሔር።

6 በእርሱም ዘመን ይሁዳ ይድናል፤እስራኤልም በሰላም ይኖራል፤የሚጠራበትም ስም፣‘እግዚአብሔር ጽድቃችን’ የሚል ነው።

7 “ስለዚህ ሰዎች፣ ‘እስራኤላውያንን ከግብፅ ምድር ያወጣ ሕያው እግዚአብሔርን!’ ብለው ከእንግዲህ የማይምሉበት ዘመን ይመጣል” ይላል እግዚአብሔር፤

8 ነገር ግን፣ ‘እስራኤልን ከሰሜን ምድርና እነርሱን ከበተነባቸው ከሌሎች አገሮች ያወጣ ሕያው እግዚአብሔርን’ ይላሉ፤ ከዚያ በኋላ በገዛ ምድራቸው ይኖራሉ።

9 ስለ ነቢያት፣ልቤ በውስጤ ተሰብሮአል፤ዐጥንቶቼም ተብረክርከዋል፤ ከእግዚአብሔር የተነሣ፣ከቅዱስ ቃሉም የተነሣ፣የወይን ጠጅ እንዳሸነፈው፣እንደ ሰካራም ሰው ሆኛለሁ።

10 ምድሪቱ በአመንዝሮች ተሞልታለች፤ከርግማን የተነሣ ምድሪቱ ታለቅሳለች፤በምድረ በዳ ያሉት መሰማሪያዎች ደርቀዋል።ነቢያቱም ጠማማ መንገድ ተከትለዋል፤ሥልጣናቸውን ያለ አግባብ ተጠቅመዋል።

11 “ነቢዩም፣ ካህኑም በጽድቅ መንገድ የማይሄዱ ናቸው፤በቤተ መቅደሴ እንኳ ሳይቀር ክፋታቸውን አይቻለሁ።”ይላል እግዚአብሔር።