ኤርምያስ 23:7-13 NASV

7 “ስለዚህ ሰዎች፣ ‘እስራኤላውያንን ከግብፅ ምድር ያወጣ ሕያው እግዚአብሔርን!’ ብለው ከእንግዲህ የማይምሉበት ዘመን ይመጣል” ይላል እግዚአብሔር፤

8 ነገር ግን፣ ‘እስራኤልን ከሰሜን ምድርና እነርሱን ከበተነባቸው ከሌሎች አገሮች ያወጣ ሕያው እግዚአብሔርን’ ይላሉ፤ ከዚያ በኋላ በገዛ ምድራቸው ይኖራሉ።

9 ስለ ነቢያት፣ልቤ በውስጤ ተሰብሮአል፤ዐጥንቶቼም ተብረክርከዋል፤ ከእግዚአብሔር የተነሣ፣ከቅዱስ ቃሉም የተነሣ፣የወይን ጠጅ እንዳሸነፈው፣እንደ ሰካራም ሰው ሆኛለሁ።

10 ምድሪቱ በአመንዝሮች ተሞልታለች፤ከርግማን የተነሣ ምድሪቱ ታለቅሳለች፤በምድረ በዳ ያሉት መሰማሪያዎች ደርቀዋል።ነቢያቱም ጠማማ መንገድ ተከትለዋል፤ሥልጣናቸውን ያለ አግባብ ተጠቅመዋል።

11 “ነቢዩም፣ ካህኑም በጽድቅ መንገድ የማይሄዱ ናቸው፤በቤተ መቅደሴ እንኳ ሳይቀር ክፋታቸውን አይቻለሁ።”ይላል እግዚአብሔር።

12 “ስለዚህ መንገዳቸው ድጥ ይሆናል፤ወደ ጨለማ ይጣላሉ፤ተፍገምግመውም ይወድቃሉ፤በሚቀጡበትም ዓመት፣መዓት አመጣባቸዋለሁ፤”ይላል እግዚአብሔር።

13 “በሰማርያ ባሉ ነቢያት ላይ፣ደስ የማያሰኝ ነገር አይቻለሁ፤በበኣል ስም ትንቢት ተናገሩ፤ሕዝቤን እስራኤልን አሳቱ።