1 የይሁዳ ንጉሥ ሴዴቅያስ በነገሠ በዐሥረኛው ዓመት፣ ይኸውም በባቢሎን ንጉሥ በናቡከደነፆር ዐሥራ ስምንተኛ ዘመነ መንግሥት፣ ከእግዚአብሔር ዘንድ ወደ ኤርምያስ የመጣው ቃል ይህ ነው፤
2 በዚያን ጊዜም የባቢሎን ንጉሥ ሰራዊት ኢየሩሳሌምን ከቦ ነበር፤ ነቢዩ ኤርምያስም በይሁዳ ንጉሥ ቤተ መንግሥት በዘብ ጠባቂዎች አደባባይ ተዘግቶበት ነበር።
3 የይሁዳ ንጉሥ ሴዴቅያስም እንዲህ በማለት አሳስሮት ነበር፤ “እንዴት እንደዚህ ያለ ትንቢት ትናገራለህ? ‘እግዚአብሔር፤ “ይህችን ከተማ ለባቢሎን ንጉሥ አሳልፌ እሰጣታለሁ፤ እርሱም ይይዛታል።
4 የይሁዳ ንጉሥ ሴዴቅያስም ለባቢሎን ንጉሥ ዐልፎ ይሰጣል፤ ፊት ለፊትም ያነጋግረዋል፤ በዐይኖቹም ያየዋል እንጂ ከባቢሎናውያን እጅ አያመልጥም።