ኤርምያስ 32:26-32 NASV

26 ከዚያም በኋላ የእግዚአብሔር ቃል ወደ ኤርምያስ እንዲህ ሲል መጣ፤

27 “እነሆ፤ እኔ የሰው ልጆች ሁሉ አምላክ እግዚአብሔር ነኝ፤ በውኑ የሚያቅተኝ ነገር አለን?

28 ስለዚህ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ እነሆ፤ ይህቺን ከተማ ለባቢሎናውያንና ለባቢሎን ንጉሥ ለናቡከደናፆር አሳልፌ እሰጣታለሁ፤ እርሱም ይይዛታል።

29 ከተማዪቱን የሚወጓት ባቢሎናውያን ወደ ውስጥ ይገባሉ፤ በእሳትም ያቃጥሏታል፤ ያስቈጡኝ ዘንድ ሕዝቡ በየሰገነቱ ላይ ለበኣል ያጠኑባቸውንና ለሌሎችም አማልክት የመጠጥ ቍርባን ያቀረቡባቸውን ቤቶች ጭምር ያነዳሉ።

30 “የእስራኤል ሕዝብና የይሁዳ ሕዝብ ከታናሽነታቸው ጀምሮ ከክፉ ነገር በቀር በፊቴ አንዳች በጎ ነገር አልሠሩም፤ በእርግጥም የእስራኤል ሕዝብ በእጃቸው ሥራ አስቈጡኝ፤ ይላል እግዚአብሔር።

31 ይህች ከተማ፣ ከተመሠረተችበት ጊዜ አንሥቶ እስከ ዛሬ ድረስ ከፊቴ እንዳስወግዳት ቍጣ ዬንና መዓቴን አነሣሥታለች፤

32 የእስራኤልና የይሁዳ ሕዝብዕጠ እነርሱ፣ ነገሥታታቸው፣ ባለሥልጣኖቻቸው፣ ካህናታቸው፣ ነቢያታቸው፣ የይሁዳ ሰዎችና የኢየሩሳሌም ነዋሪዎች ባደረጉት ክፋት ሁሉ አስቈጡኝ።