1 ኤርምያስ ለሕዝቡ የተናገረውን ቃል የማታን ልጅ ሰፋጥያስ፣ የጳስኮር ልጅ ጎዶልያስ፣ የሰሌምያ ልጅ ዮካል እንዲሁም የመልክያ ልጅ ጳስኮር ሰሙ፤ ቃሉም እንዲህ የሚል ነበር፦
2 “እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ‘በዚህች ከተማ የሚቀር ሁሉ በሰይፍ፣ በራብ ወይም በቸነፈር ይሞታል፤ ይህን ስፍራ ለቆ ወደ ባቢሎናውያን የሚሄድ ሁሉ ይተርፋል፤ ያመልጣል፤ በሕይወትም ይኖራል።’
3 እግዚአብሔርም እንዲህ ይላል፤ ‘ይህች ከተማ በእርግጥ ለባቢሎን ንጉሥ ሰራዊት ዐልፋ ትሰጣለች፤ እርሱም ይይዛታል።’ ”
4 መኳንንቱም ንጉሡን እንዲህ አሉት፤ “ይህ ሰው በሚናገረው ነገር በዚህች ከተማ የቀሩትን ወታደሮችና ሕዝቡንም ሁሉ ተስፋ የሚያስቈርጥ ስለ ሆነ መሞት አለበት፤ ይህ ሰው የሕዝቡን መጥፋት እንጂ መልካም ነገር አይሻም።”