ኤርምያስ 39:4-10 NASV

4 የይሁዳ ንጉሥ ሴዴቅያስና ወታደሮቹ ሁሉ እነርሱን ባዩ ጊዜ ሸሹ፤ በሌሊት በንጉሡ አትክልት ስፍራ በኩል አድርገው በሁለቱ ቅጥር መካከል ከከተማዪቱ ወጡ፤ ወደ ዓረባም አመሩ።

5 የባቢሎን ሰራዊት ግን ተከትሎ አሳደዳቸው፣ በኢያሪኮም ሜዳ ደርሶባቸው ሴዴቅያስን ያዘ፤ ማርከውም በሐማት ምድር ወዳለችው ወደ ሪብላ ወደ ባቢሎን ንጉሥ ወደ ናቡከደነፆር አመጡት፤ በዚያም ፍርድ ወሰነበት።

6 የባቢሎንም ንጉሥ በሪብላ የሴዴቅያስን ወንዶች ልጆች፣ አባታቸው እያየ ዐረዳቸው፤ የይሁዳን መሳፍንት ሁሉ ገደላቸው፤

7 የሴዴቅያስንም ዐይኖች አወጣ፤ ወደ ባቢሎን ሊወስደውም በናስ ሰንሰለት አሰረው።

8 ባቢሎናውያን ቤተ መንግሥቱንና የሕዝቡን ቤት በእሳት አቃጠሉ፤ የኢየሩሳሌምንም ቅጥር አፈረሱ።

9 የባቢሎን መንግሥት የክብር ዘበኞች አዛዥ ናቡዘረዳን፤ በከተማዪቱ የቀረውን ሕዝብ ሁሉ ማርኮ ወደ ባቢሎን ወሰዳቸው።

10 ንብረት ያልነበራቸውን ድኾች ግን የክብር ዘበኞች አዛዥ ናቡዘረዳን፣ በይሁዳ ምድር ተዋቸው፤ በዚያ ጊዜም የወይን አትክልት ቦታና የዕርሻ መሬት ሰጣቸው።