6 የባቢሎንም ንጉሥ በሪብላ የሴዴቅያስን ወንዶች ልጆች፣ አባታቸው እያየ ዐረዳቸው፤ የይሁዳን መሳፍንት ሁሉ ገደላቸው፤
7 የሴዴቅያስንም ዐይኖች አወጣ፤ ወደ ባቢሎን ሊወስደውም በናስ ሰንሰለት አሰረው።
8 ባቢሎናውያን ቤተ መንግሥቱንና የሕዝቡን ቤት በእሳት አቃጠሉ፤ የኢየሩሳሌምንም ቅጥር አፈረሱ።
9 የባቢሎን መንግሥት የክብር ዘበኞች አዛዥ ናቡዘረዳን፤ በከተማዪቱ የቀረውን ሕዝብ ሁሉ ማርኮ ወደ ባቢሎን ወሰዳቸው።
10 ንብረት ያልነበራቸውን ድኾች ግን የክብር ዘበኞች አዛዥ ናቡዘረዳን፣ በይሁዳ ምድር ተዋቸው፤ በዚያ ጊዜም የወይን አትክልት ቦታና የዕርሻ መሬት ሰጣቸው።
11 የባቢሎን ንጉሥ ናቡከደነፆር በክብር ዘበኞቹ አዛዥ በናቡዘረዳን በኩል ስለ ኤርምያስ እንዲህ የሚል ትእዛዝ ሰጠ፤
12 “ውሰደውና እንክብካቤ አድርግለት፤ የሚፈልገውን ነገር ፈጽምለት እንጂ አትጒዳው።