1 ኤርምያስ፣ እግዚአብሔር ለእነርሱ እንዲነግራቸው የላከውን የአምላካቸውን የእግዚአብሔርን ቃል ሁሉ ለሕዝቡ ተናግሮ በጨረሰ ጊዜ፣
2 የሆሽያ ልጅ ዓዛርያስ፣ የቃሬያ ልጅ ዮሐናንና ትዕቢተኞች የሆኑ ሰዎች ሁሉ ኤርምያስን እንዲህ አሉት፤ “ትዋሻለህ! አምላካችን እግዚአብሔር፣ ‘እዚያ ለመኖር ወደ ግብፅ አትሂዱ ብለህ ንገራቸው’ ብሎ አልላከህም፤
3 ነገር ግን ባቢሎናውያን እንዲገድሉን ወይም ማርከው ወደ ባቢሎን እንዲወስዱን ለእነርሱ አሳልፈህ ትሰጠን ዘንድ የኔርያ ልጅ ባሮክ በእኛ ላይ አነሣሥቶሃል።”
4 ስለዚህ የቃሬያ ልጅ ዮሐናንና፣ የጦር መኰንኖቹ ሁሉ እንዲሁም ሕዝቡ በሙሉ እግዚአብሔር በይሁዳ ምድር እንዲቀመጡ ያዘዛቸውን ቃል አልሰሙም።
5 ነገር ግን፣ የቃሪያ ልጅ ዮሐናንና የጦር መኮንኖቹ ሁሉ፣ በይሁዳ ምድር ለመቀመጥ ከተበተኑበት ከአሕዛብ ሁሉ መካከል የተመለሱትን የይሁዳን ቅሬታዎች ሁሉ ይዘው ሄዱ፤
6 በተጨማሪም ወንዶችን፣ ሴቶችንና ሕፃናትን እንዲሁም የክብር ዘበኞች አዛዥ ናቡዘረዳን በአኪቃም ልጅ በጎዶልያስ እጅ የተዋቸውን የንጉሡን ሴቶች ልጆች፣ ነቢዩ ኤርምያስንና የኔርያን ልጅ ባሮክን ወሰዷቸው፤
7 የእግዚአብሔርንም ቃል ባለመታዘዝ ወደ ግብፅ ገቡ፤ ዘልቀውም እስከ ጣፍናስ ድረስ ሄዱ።