ኤርምያስ 46:13-19 NASV

13 የባቢሎን ንጉሥ ናቡከደናፆር መጥቶ ግብፅን እንደሚወጋ፣ እግዚአብሔር ለነቢዩ ለኤርምያስ የተናገረው መልእክት ይህ ነው፤

14 “ይህን በግብፅ ተናገር፤ በሚግዶልም አሰማ፤በሜምፎስና በጣፍናስም እንዲህ ብለህ ዐውጅ፤በቦታችሁ ቁሙ፤ ተዘጋጁም፤በዙሪያችሁ ያሉትን ሰይፍ ይበላቸዋልና።

15 ጦረኞችህ ለምን ተዘረሩ? እግዚአብሔር ገፍትሮ ስለሚጥላቸው መቆም አይችሉም።

16 ደጋግመው ይሰናከላሉ፣አንዱም በሌላው ላይ ይወድቃል፤‘ተነሡ እንሂድ፤ወደ ሕዛባችንና ወደ ትውልድ አገራችን እንመለስ፤ከጠላትም ሰይፍ እናምልጥ’ ይላሉ።

17 በዚያም የግብፅን ንጉሥ ፈርዖንን፣በተሰጠው ዕድል ያልተጠቀመ፣አለሁ አለሁ ባይ ደንፊ!’ ብለው ይጠሩታል።

18 ስሙ የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር የሆነው ንጉሡ እንዲህ ይላል፤በሕያውነቴ እምላለሁ።በተራሮች መካከል ያለውን የታቦር ተራራ የሚመስል፣ባሕርም አጠገብ ያለውን የቀርሜሎስ ተራራ የሚመስል አንድ የሚመጣ አለ።

19 እናንተ በግብፅ የምትኖሩ ሆይ፤በምርኮ ለመወሰድ ጓዛችሁን አሰናዱ፤ሜምፎስ ፈራርሳ፣ሰው የማይኖርባት ባድማ ትሆናለችና።