ኤርምያስ 52:15-21 NASV

15 የዘቦቹ አዛዥ ናቡዘረዳን አንዳንድ ድኾችንና በከተማዪቱ የቀረውን ሕዝብ፣ የእጅ ጥበብ ያላቸውንና ሸሽተው ወደ ባቢሎን ንጉሥ የተጠጉትን አፈለሳቸው።

16 ነገር ግን የክብር ዘበኞቹ አዛዥ ናቡዘረዳን ሌሎች የምድሪቱን ድኾች ወይን ተካዮችና ዐራሾች እንዲሆኑ አስቀራቸው።

17 ባቢሎናውያን በእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ የነበሩትን የናስ ዐምዶች፣ ተንቀሳቃሽ ማስቀመጫዎችንና ከናስ የተሠራውን የውሃ ገንዳ ሰባበሩ፤ ናሱንም ሁሉ ወደ ባቢሎን ይዘው ሄዱ።

18 ከእነዚህም ሌላ ምንቸቶቹን፣ መጫሪያዎቹን፣ መኰስተሪያዎቹን፣ ወጭቶችን፣ ጭልፋዎቹንና ለቤተ መቅደስ አገልግሎት የሚውሉትን የናስ ዕቃዎች በሙሉ ወሰዱ።

19 የክብር ዘበኞቹ አዛዥ ከንጹሕ ወርቅና ከንጹሕ ብር የተሠሩትን ዕቃዎች ሁሉ ጐድጓዳ ሳሕኖችን ጥናዎችን፣ ወጭቶችን፣ ምንቸቶችን፣ መቅረዞችን፣ ጭልፋዎችንና ለመጠጥ ቍርባን ማቅረቢያ የሚሆኑ ወጭቶችን ይዞ ሄደ።

20 ንጉሥ ሰሎሞን ለእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ከናስ ያሠራቸው፦ ሁለቱ ዐምዶች፣ ትልቁ የውሃ ገንዳ፣ ከሥሩ ያሉት ዐሥራ ሁለት ወይፈኖችና ተንቀሳቃሽ ማስቀመጫዎች ክብደታቸው ሚዛን ከሚችለው በላይ ነበር።

21 እያንዳንዱም ዐምድ ከፍ ታውዐሥራ ስምንት ክንድ ዙሪያ ክቡም ዐሥራ ሁለት ክንድ ነበረ፤ ውስጡ ክፍት ስለ ሆነ የእያንዳንዱ ከንፈር ውፍረት አራት ጣት ነበረ።