3 እግዚአብሔር በኢየሩሳሌምና በይሁዳ ላይ ይህን ሁሉ ያደረሰውንና በመጨረሻም ከፊቱ ያስወገዳቸው ከቍጣው የተነሣ ነበር።ሴዴቅያስም በባቢሎን ንጉሥ ላይ ዐመፀ።
4 ስለዚህ ሴዴቅያስ በነገሠ በዘጠነኛው ዓመት በዐሥረኛው ወር፣ ከወሩም በዐሥረኛው ቀን፣ የባቢሎን ንጉሥ ናቡከደነፆር ሰራዊቱን ሁሉ አስከትቶ በኢየሩሳሌም ላይ ዘመተ፤ ከተማዪቱንም ከበቧት፤ በዙሪያውም የዐፈር ድልድል ሠሩ።
5 ከተማዪቱም እስከ ንጉሡ እስከ ሴዴቅያስ ዐሥራ አንደኛ ዘመነ መንግሥት ተከባ ነበር።
6 በአራተኛው ወር በዘጠነኛው ቀን በከተማዪቱ ራብ ጸንቶ ስለ ነበር ሕዝቡ የሚበላውን አጣ፤
7 የከተማዪቱም ቅጥር ተነደለ፤ ሰራዊቱም ሁሉ ኰብልሎ ሄደ። ባቢሎናውያን በከተማዪቱ ዙሪያ ቢኖሩም፣ በንጉሡ የአትክልት ስፍራ አጠገብ በሁለት ቅጥሮች መካከል ባለው በር በሌሊት ከተማዪቱን ጥለው ሸሹ፤ ወደ ዓረባም አመሩ።
8 የባቢሎናውያንም ሰራዊት ንጉሥ ሴዴቅያስን ተከታትሎ በማሳደድ በኢያሪኮ ሜዳ ደረሱበት፤ ወታደሮቹም ሁሉ ከእርሱ ተለይተው ተበታትነው ሳለ፣ ንጉሡን ያዙት።
9 እርሱም በሐማት ምድር በሪብላ ወደ ነበረው ወደ ባቢሎንም ንጉሥ ተወሰደ፤ የባቢሎን ንጉሥ በዚያ ፈረደበት።