ኤርምያስ 7:26-32 NASV

26 ሕዝቡ ግን አልሰማኝም፤ ልብ ብሎ ለማድመጥም አልፈለገም፤ ዐንገታቸውን አደነደኑ አባቶቻቸው ከሠሩት የባሰም ክፉ አደረጉ።” ’

27 “ይህን ሁሉ ትነግራቸዋለህ፤ እነርሱ ግን አይሰሙህም፤ ትጠራቸውማለህ፤ አይመል ሱልህም።

28 ስለዚህ እንዲህ በላቸው፤ ‘ይህ ሕዝብ አምላኩን እግዚአብሔርን ያልታዘዘ፣ ምክሩን ያልተቀበለ ወገን ነው፤ እውነት ጠፍቶአል፤ ከአንደበታቸውም ሸሽቶአል።

29 እግዚአብሔር ቍጣው የወረደበትን ይህን ትውልድ ስለ ናቀውና ስለ ተወው፣ ጠጒርሽን ቈርጠሽ ጣይ፤ በባድሞቹ ኰረብቶች ላይ ሆነሽም ሙሾ አውጪ።

30 “ ‘የይሁዳ ሕዝብ በፊቴ ክፉ ነገር አድርጓል፤ ይላል እግዚአብሔር፤ አስጸያፊ ነገራቸውን ስሜ በተጠራበት ቤት በማስቀመጥ አርክሰውታል።

31 እኔ ያላዘዝኋቸውን፣ ከቶም ያላሰብሁትን ወንዶችና ሴቶች ልጆቻቸውን በእሳት አቃጥለው ለመሠዋት በሄኖም ልጅ ሸለቆ የቶፌትን መስገጃ ኰረብቶች ሠሩ።

32 ስለዚህ አስተውሉ፤ ይላል እግዚአብሔር፤ ስፍራ እስከማይገኝ ድረስ ሙታንን በቶፌት ስለሚቀ ብሩ፣ የዕርድ ሸለቆ እንጂ ከእንግዲህ ቶፌት ወይም የሄኖም ልጅ ሸለቆ ተብሎ የማይጠራበት ጊዜ ይመጣል።