16 “ስለ እርሷ የሚያወርዱት ሙሾ ይህ ነው፤ የሕዝቦች ሴት ልጆች ያዜሙታል፤ ስለ ግብፅና ስለ ብዙ ሰራዊቷ ሁሉ ሙሾ ያወርዳሉ፤ ይላል ጌታ እግዚአብሔር።”
17 በዐሥራ ሁለተኛው ዓመት፣ ከወሩም በዐሥራ አምስተኛው ቀን የእግዚአብሔር ቃል እንዲህ ሲል ወደ እኔ መጣ፤
18 “የሰው ልጅ ሆይ፤ ስለ ብዙው የግብፅ ሰራዊት አልቅስ፤ እርሷንና የኀያላንን ሕዝቦች ሴት ልጆች ወደ ጒድጓድ ከሚወርዱት ጋር ከምድር በታች አውርዳቸው።
19 እንዲህም በላቸው፤ ‘እናንተ ከሌሎች የተለያችሁ ናችሁን? ውረዱ፤ ባልተገረዙትም መካከል ተጋደሙ።’
20 እነርሱም በሰይፍ በተገደሉት መካከል ይወድቃሉ፤ ሰይፉ ተመዟል፤ ከብዙ ሰራዊቷ ሁሉ ጋር ትጐተት።
21 በመቃብርም ውስጥ ኀያላኑ መሪዎች ስለ ግብፅና ስለ ተባባሪዎቿ፣ ‘ወደ ታች ወርደዋል፤ በሰይፍ ከተገደሉትና ካልተገረዙትም ጋር በአንድ ላይ ተጋድመዋል’ ይላሉ።
22 “አሦር ከመላው ሰራዊቷ ጋር በዚያ ትገኛለች፤ በሰይፍ በወደቁባትና በታረዱባት ሰዎች ሁሉ መቃብር ተከባለች።