ሕዝቅኤል 34:7-13 NASV

7 “ ‘ስለዚህ እናንት እረኞች፣ የእግዚአብሔርን ቃል ስሙ፤

8 በሕያውነቴ እምላለሁ፣ ይላል ጌታ እግዚአብሔር፤ እረኞቼ መንጋዬን ስላልፈለጉ፣ ከመንጋዬም ይልቅ ራሳቸውን ስለተንከባከቡ፣ መንጋዬ እረኛ አጥቶ ለንጥቂያ ተዳርጎአል፤ ለአራዊትም ሁሉ መብል ሆኖአል።

9 ስለዚህ እረኞች ሆይ፤ የእግዚአብሔርን ቃል ስሙ፤

10 ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ እኔ በእረኞች ላይ ተነሥቻለሁ፤ ስለ መንጋዬ እጠይቃቸዋለሁ፤ ከእንግዲህ እረኞች ራሳቸውን መመገብ እንዳይችሉ፣ መንጋዬን እንዳያሰማሩ አደርጋለሁ። መንጋዬን ከአፋቸው አስጥላለሁ፤ ከእንግዲህም ምግብ አይሆናቸውም።

11 “ ‘ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላልና፤ እኔ ራሴ በጎቼን እፈልጋቸዋለሁ፤ እጠብቃቸዋለሁም።

12 እረኛ ከመንጋው ጋር ሳለ፣ የተበተኑበትን በጎች እንደሚፈልግ ሁሉ፣ እኔም በጎቼን እፈልጋለሁ። በደመናና በጨለማቀን ከተበተኑበት ስፍራ ሁሉ አድናቸዋለሁ።

13 ከአሕዛብ መካከል አወጣቸዋለሁ፤ ከየአገሮቹ እሰበስባቸዋለሁ፤ ወደ ገዛ ምድራቸውም አመጣቸዋለሁ። በእስራኤል ተራሮች፣ በየወንዙ ዳርና፣ በምድሪቱ መኖሪያዎች ሁሉ እንዲሰማሩ አደርጋለሁ።